Saturday, November 08, 2008

“የኦባማ ትንግርትና ዳያስፖራው!”
ባሜሪካው ትንግርትና በበራክ ኦባማ መመረጥ ያልተደነቀና ያልፈነደቀ የዴሞክራሲ ወዳጅ ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም። በውጥረት የተከበበች ዓለምና ተስፋ እየራቀው የመጣ ሕዝብ ሁሉም ማለፊያ ሊሆን እንደሚችል የሚያረጋግጥለት ድምጽ ሲያገኝ ደስ ይላል።

ይህ እንዳለ ሆኖ ከዛሬው ፈንጠዝያና ግርግር ባሻገር የምናገኘውን መጠነ ሰፊ ትምህርት እንዳንስት እሰጋልሁ። ትምህርቱ ላሜሪካኖች ብቻ የመጣ ሳይሆን ያለም ዳርቻን ያዳረሰ አዋቂውንና ምሁሩን ሁሉ አፍ ያስከፈተ የሚሊኒየም አርዓያ ስለሆነ ነው።

የኦባማ ትንግርት አይቀሬ የትውልድ ርክክብና የዘመን ሺግግር የታወጀበት ለመሆኑ አያጠራጥርም። አሜሪካ ይኑር ኢትዮጵያ፤ አውስትራሊያ ይኑር ብራዚል፤ የዚህ የ21ኛው ክፍለዘመን ትውልድ አመለካከትና የትኩረት አቅጣጫ ከኛው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ለማዬት በቅተናል። ያረጀ ርዕዮት በአዲስና ወደፊት ብቻ በሚመለከት ርዕዮት መቀየር እንዳለበት ተረድተናል። የቆዳ ቀለም፤ የብሔር መሠረትና ሌሎቹም ኋላ ቀር አመለካከቶች አሳፋሪ ቅርሶች እንደሆኑ በማያሻማ ቋንቋ ተነግሮናል። አዲሱ ትውልድ የስጋት ዘንግ በመስበቅ፤ የጥርጣሬ መርዝ በመዝራት፤ ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት እንደማይደነብርና እንደማይበገር አሳውቆናል። የማኪያቬሊን መጽሀፍ ሲያነበንቡ የሚያድሩና የፖለቲካ እንዝርት ሲያሽከረክሩ የሚውሉ ገዥዎች ዘመናቸው እንዳበቃ ይህ ትውልድ በራክ ኦባማን በመምረጥ አውጇል።

በትንሿ በራሴ ቤት እንኳ ተአምር ለማየት በቅቻለሁ። የ23 ዓመቱ ልጄ ኦባማ ጋሪ ላይ የተሳፈረው ከመነሻው ነበር። የ4ኛ ዓመት ኮሌጅ ተማሪ ቢሆንም ቅዳሜና እሁዱን፤ ሌላም ትርፍ ጊዜውን ለበራክ ዳረገ። ይህን አገኛለሁ ብሎ ሳይሆን ለኔና ለመሰሎቼ ያልተሰማን የትውልድ ቃጭል ጥሪ ተሰምቶት። እልም ባለ በረዶና በበጋው ወበቅ ከኒው ሃምሸር እስከ ቨርጂኒያ በራሱ ገንዘብ እየተጓዘ የማያውቃቸውንና የማያውቁትን ሰዎች ቤት አንኳኳ። ባራክንና ፕሮግራሙን አስተዋወቀ፤ አሳመነ፤ ስልጡን ሙግት ተሟገተ፤ ግልምጫ ቀመሰ፤ ተጠራጠረ፤ እንደገና ደግሞ አመነ። ተማረ.. ብዙ ተማረ።

ከምንምና ከማንም ይበልጥ እንቅልፉን ሲወድ የማውቀው ብላቴና፤ ሰዎች በፖለቲካ ውይይት ተጠምደው ሲያይ ከሞኝ ይቆጥር የነበረ ወጣት፤ ና እንግዳ ተዋወቅ ሲሉት መኝታ ቤቱ ውስጥ የሚታሺ ልጅ፤ አይፖዱን ጆሮው ላይ ሰክቶ እራሱን ኬሌላው ዓለም ያገለለው “ማይክ” ዛሬ ግፊቱንና ወኔውን ከየት እንዳገኘው ሳሰላስል እራሴ ይዞራል። በኔ የሀያ ዓመት ጭቅጭቅና ማባበል ያልተበገረ ቆዳና አዕምሮ በዚህ ዘመን በነፈሰ አየር ፈክቶና አብቦ አገኘሁት።

ይህ በጎ አየር ያወደው የኔውን ቤት ብቻ ሳይሆን መላ ሕብረተሰቡንና መላ የወጣቱን ትውልድ እንደሆነ የተረዳሁት ወዲያውኑ ነው። ፈረንጁና ጥቁሩ፤ ሂስፓኒኩና ኦሪየንታሉ፤ ወጣቱና ሽማግሌው፤ ሴቱና ወንዱ በኦባማ ፕላትፎርም አማካይነት አንድ አካልና አንድ አምሳል ሆነው፤ ያንድ አገር ዜጋና ያንድ ብሩህ ተስፋ ባለቤት ሆነው፤ እንደ አንደ ትልቅ ሠራዊት ተንቀሳቅሰው ኦባማን አስመረጡት።

አገራቸው የምትጓዝበትን የስግብግብነት፤ የጥፋት፤ የጥርጣሬና የጥላቻ ሀዲድ ፍቅር መተሳሰብና ሰብአዊነት ተዋህደው በፈጠሩት ሀዲድ ለወጡት። ባውሮፕላን ተበሮ በመኪና ተንድቶ ማለቂያ በማይገኝለት፤ ያዳም ዘር ዓይነት በሚተራመስበት የሦስት መቶ ሚሊዮን ዜጎች ቤት ይህ የሥልጣንና የትውልድ ሺግግር ሲፈጸም አንዲት ጥይት አልተተኮሰችም፤ አንዲት ቦምብ አልፈነዳችም። ተሸናፊው ማኬን የበራክን ማሸነፍ ተቀብለው መድረኩን ሲለቁ ያደረጉት ንግግር ልብ የሚነካ ብቻ ሳይሆን ስልጡን ፖለቲካ የቱን ያህል ስልጡን እንደሆነ የሚያመለክት ነበር። ለማኬን ከቀድሞ የበለጠ አክብሮት ሰጠኋቸው። ላሜሪካ የዴሞክራሲ ባህል ያላደርግሁትን ባርኔጣ አነሳሁለት። የዕለቱን ግዙፍነትና ምሳሌነት እንደተረዱ ሰዎች ሁሉ እንባዬ ሲንከባለል አገኘሁት። በዚህ ታሪካዊ የሺግግር ወቅት በህይወት መኖሬን ወደድሁት፤ ታሪክ ተመልካች ብቻ ሳልሆነ ያቅሜን ተሳትፌ የታሪኩ አካልና ባለቤት ሆንኩ። እኔና ልጆቼ ለመጀመሪያ ጊዜ ያንድ ዕምነትና ያንድ አስተሳሰብ ማሕበርተኞች ሆነን ጥዋ ጠጣን። ለዚህም ፀጋ ፈጣሪየን አመሰገንሁት። ከልቤ።

ስለ ኢትዮጵያዊው ሕብረተሰብ በጥቂቱ ላንሳ። ኢትዮጵያዊው ኦባማን የደገፈው በሙሉ ልቡ ብቻ ሳይሆን ለጊዜውና ለኪሱ ሳይሳሳ ነበር። በካምፔይኑ ቢሮዎች በፈቃደኝነት እየተገኘ የ “ምረጡ!” ስልክ የደወለው፤ ከቤት ቤት እየዞረ የቀሰቀሰው፤ ደካሞችን በግል መኪናው ወደምርጫ ጣቢያ ያመላለሰው ሀበሻ ብዛት ያመሪካኖቹንም የሚዲያውንም ቀልብ ስቧል። ባማርኛ የተጻፉ ማስታዎሻዎች፤ ስሞችና የመልካም ምኞት መግለጫዎች በካምፔይን ቢሮዎች ማዬት የተለመደ ብቻ ሳይሆን ላሜሪካ ሕብረቀለማዊ ውበት የበለጠ ድምቀት ያጎናጸፈ ነበር። በዚህ የተሳትፎ መጠን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በየመሥሪያ ቤቱ በተሿሚነት ብቅ ብቅ ቢሉ ልንደነቅ አይገባም።

ኢትዮጵያዊው ባሜሪካው ምርጫ እንዲህ በጋለ ስሜት የተሳተፈበት ምክንያት ለኔ ግልጽ ነው። ዳያስፖራዊው ዴሞክራሲን በትውልድ አገሩ ለማየት ከፍተኛ ትግል ያካሄደና ብዙ መሰዋዕትነት የከፈለ ነው። ባገሩ ያላገኘውን ፀጋ ዛሬ በሰው አገር ሆኖ ቀመሰው። በየካምፔይኑ ቢሮ ሲሯሯጥ፤ ያለክፍያ ሲለፋና የውድድሩን ዕድገት በአንክሮ ሲከታተል እናት አገሩንና ወገኑን እያስታወሰ ለመሆኑ አልጠራጥርም። ይህ ወግ አንድ ቀንና በቅርቡ የወገኑ እንዲሆን እየተመኘና ከህሊናው ጋር ቃል ኪዳን እየገባ ነው።

የኦባማ ትንግርት የዳያስፖራውም ድል ነው ስል ምክንያት አለኝ። በዚህ የምርጫ ጉዞ ውስጥ ወገኔ የበለጠ ዕውቀት፤ የበለጠ ልምድ፤ የበለጠ ወዳጅና ዘርፈ-ብዙ የግንኙነት መሥመሮች ዘርግቷል። የፖለቲካ ካፒታል አከማችቷል። ይህ ዕውቀት ይህ ግንኙነትና ይህ የፖለቲካ ካፒታል በሚያስፈልግበት ጊዜ የሚመነዘር ሀብት ነው። የዳያስፖራው የዴሞክራሲ ንቅናቄና ማህበራዊ ፕሮግራሞች በደለበ ልምድ፤ በሰላ ማኔጅመንትና በዘመናዊ ቴክኖሎጅ ተደግፈው ሲመሩ ይታየኛል። ይህ ልምድና የጋለ ስሜት ወደ ሀገር ቤት ሲዛመት ደግሞ በኢትዮጵያ አዲስ ዘመን ይሆናል።

kuchiye@gmail.com