Saturday, June 13, 2009


"የግልገል ግቤ-3 እና የላሟ ታሪክ!"

“ላም እሳት ወለደችና እንዳትልሰው እሳት እንዳትተው ልጇ ሆነ!”
ይህ አባባል ግለሰቦችም ማሕበረሰቦችም በኑሮ ሂደት ውስጥ አስጨናቂ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚገደዱባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚያመለክት ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ብንዘጋቸው የማይዘጉ፤ መልስ እስካላገኙ ድረስ ከፊታችን ዞር የማይሉ ችኰ ነገሮች ናቸው። 3ኛው የግልገል ግቤ ፕሮጀክት እንዲህ ሆኖብን ስለከረመ እንደልማዴ የማውቀውንና የሚሰማኝን ላካፍላችሁ መረጥሁ፡
ስለ ግቤ
ግቤ የተንጣለለውን የኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ክፍል እያካለለ መልኩን አሳምሮ ወደ ኬንያ ዳርቻ የሚነጉድ ወንዝ ነው። ታዲያ እርባና ያለው ሕይዎት ሳይኖር ቆይቶ በደርጉ ዘመን ሠርተህ ብላ ተባለ። ከዚያ በኋላ ግቤ-1 እና ግቤ-2 የሚባሉ ፕሮጀችቶች ተከናውነው 400 ሜጋዋት ኤለክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ተገንብቷል። ግቤ-2 ፍጻሜ ያገኘው በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት መሆኑን መግለጽ ተገቢ ይመስለኛል።
ግልገል ግቤ-3
የግልገል ግቤ-3 ፕሮጀክት ፅንሰ-ሀሳብ በአፍሪካ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው የኤሌክትሪካ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በመገንባት ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ ግብጹ “አስዋን” ዳም ለኢትዮጵያ የልማት ሞተር ሊሆን የሚችል ሃይል ለመፍጠር ማለት ነው። የፕሮጀክቱ ሥራ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚፈጅ ሲገመት በሚጠናቀቅበት ጊዜ 1870 ሜጋዋት እሌክትሪሲቲ ያመነጫል። ለንጽጽር እንዲረዳችሁ ያሁኑ የኢትዮጵያ አቅም የሚያሳዝን 600 ሜጋዋት ብቻ ነው። ለዚህ ነው አገራችን በኩራዝ የምትኖረው። ለዚህም ነው ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ሳትቀር በሳምንት ለሦስት ቀን የኮረንቲ ራሽን የተዳረገችው። ግልገል ግቤ-3 ካገሪችን ተርፎ ለጎረቤት አገሮችም የመሸጥ አቅም እንደሚያስገኝ ይነገራል።

ታዲያ ከባድ ችግር ተፈጥሮላችኋል! የግቤ ወንዝ ውልደቱም ጉልምስናውም እርጅናውም ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ እያለ ኢትዮጵያ በዚህ ወንዝ እንዳሻት ልትጠቀም አትችልም የሚሉ ጉዶች ፈልተዋል። “በገዛ ዳቦዬ ልብ-ልቡን አጣሁት” ዓይነት ነገር መሆኑ ነው። እንዳሸን መፍላት ብቻ ሳይሆን ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ኢትዮጵያ እናዳትበደር እያከላከሉም ነው። ግብጽና ሱዳን በግልገል ግቤ-3 ታላቅነት ተደናግጠዋል (ኬንያም እንዲሁ)። ኤንቫይሮንሜንታሊስቶች የሚያናፍሱት አጀንዳና የሚያፍሱት ዶላር በማግኘታቸው ፈንድቀዋል፤ እኛ ደግሞ በነገሩ ግራ ተጋብተን የላሟን ዓይነት ሆነናል። ሦስቱንም በየተራ ላስረዳ።
ግብጽና ሱዳን
በምናውቀው ምክንያት ግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያን መጎልበት አይፈልጉም። ጠንካራ ኢትዮጵያ ማለት ካባይ ወንዝ ላይ ድርሻዋን የምትጠይቅ ኢትዮጵያ ትሆንባቸዋለችና ወደሠላምና ወደብልጽግና የሚወስዳትን ጎዳናዎች ሁሉ በፈንጅ ከማጠር አይቦዝኑም። ያባይ ወንዝ መነሻውን እስካልለወጠ ድረስ ከነዚህ አገሮች ጋር ያለን ባላንጣነት ይቀጥላል። ይህ ያጉል ተጠራጣሪ አመለካከት ሳይሆን (ኮንስፒረሲ ቲዎሪስት አለመሆኔን ታውቃላችሁና) ግብጦችም ደርቡሾችም በሰነዘሩብን ተደጋጋሚ ጦርነትና ባሴሩብን ሴራ መጎዳታችን በታሪክ የተመሰከረ ነው።

ግብጾች የግቤ-3ን ፕሮጀክት ለማሰናከል ጥድፊያ ላይ ናቸው ይባላል። በውሀ አጠቃቀም ሕግ የተራቀቁ ናቸው የሚባልልላቸው ድርጅቶቻቸው፤ ምሁራኖቻቸውና የዲፕሎማቲክ ጡንቻቸው የግቤ-3 ፕሮጀክትን “ጐጅነት” በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ። የውሮፓ ኢንቬትመንት ባንክ፤ ዓለም ባንክና አሁን ደግሞ ያፍሪካ ልማት ባንክ ለግቤ-3 ገንዘብ እንዳያበድሩ ከኤንቫይሮንሜንታሊስቶች ጀርባ ሆነው ዘመቻ እያካሄዱ ነው። ዘመዶቼ! ግብጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነት ቀላል እንዳልሆነ ምንጊዜም መዘንጋት የለብንም ።
የኤንቫይሮሜንታሊስቶች ጫጫታ!
ኤንቫይሮንሜንታሊስቶች ጥሩ ጎን ያላቸውን ያህል አንዳንዱ ባሕርያቸው አስቂኝ ነው። ግቤ-3ን በሚመለከት ግድቡ ከተሠራ ያካባቢው ነዋሪ ሕዝብ ኑሮ ይበላሻል ይላሉ። ኤኮሎጅ ይናጋል ይላሉ። እስኪ በፈጠራችሁ የትኛው የኑሮ ዓይነት ነው የሚበላሸው? መለ-መላ የሚኬድበት? ከንፈር የሚተለተልበት? ረሀብ፤ ድንቁርና፤ መሀይምነትና በሽታ የነገሱበት? ወይንስ ደግሞ ጥቂት ቱሪስቶች የፎቶ አጋጣሚ አግኝተው የበላይነት ስሜት የሚገዙበት?

ቢማሮ አምደልካር የተባለው ከጋንዲ የሚተካከል የህንድ አባት “ምሁሩ በገጠሩ ላይ ያለው ፍቅር ማለቂያ የሌለው ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው” ይልና “በሀቅ ከተመለከትነው ገጠሩ የድንቁርናና የበሽታ ጉሮኖ፤ የጎሰኝነት ኩሬ፤ የጠባብ አመለካከት ጎተራ ነው” ብሎ ይደመድማል። እኔ ደግሞ “ኋላቀር የኑሮ ዘይቤዎችን አላግባብ የሚያወድሱና ከዘመናችን የኑሮ ዘይቤ ጋር መሳ-ለመሳ ለማስቀመጥ የሚሞክሩ እነርሱ ጤነኞች አይደሉም ደህና ሀኪም ያስፈልጋቸዋል።” እላለሁ

ስለ ኤንቫይሮንሜንት ካነሳን ዘንድ የዓለም ሥልጣኔ አስቸጋሪና አስቸጋሪ ያልሆኑ ምርጫዎችን እያደረገ ነው እዚህ የደረሰው። አሜሪካ፤ አውሮፓና እስያ የተገነቡት ኤንቫይሮንሜንት ሳይቀየር አይደለም። ሁቨር፤ አስዋን፤ ሜርዌ፤ ያንግቴዝና ሌሎችም እርቆ መሳፍርት የሌላቸው ግድቦችና ልማቶች ሲከናወኑ ሰፋፊ መሬቶች በውሀ መጥለቅልቅ ነበረባቸው። የታሪክ ቅርሶችና ማዕድኖች ሳይቀሩ በሐይቆቹ ሥር ማቅረታቸው አማራጭ አልነበረውም። እነዚህ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በመለወጥ በኩል ያደረጉት አስተዋጽኦ ግዙፍ ነውና ክርክር እንኳ አይጠይቅም።

ልብ በሉ። የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ኤንቫይሮንሜንት ሁለተኛ ደረጃ ትኩረት ነው የሚያገኘው። በኔ ግምት ግቤ-3 ለኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው። የሚያወላዳ ሀብት ለሌላትና በመጨረሻው የድህነት እርከን ላይ ለምትገኝ ኢትዮጵያ “ኤሌክትሪፊኬሽን” አማራጭ የሌለው የልማት ርምጃ ስለሆነ የትኛውም መንግሥት ሥልጣን ላይ ቢሆን ወደኋላ የሚባልበት ጉዳይ አይሆንም። የምናዘገዬው ጉዳይም አይደለም።
ታዲያ ምኑ ነው እኛን ግራ ያጋባን?
እኛን ግራ ያጋባን የኢሕአዴግ ጉዳይ ነው። ኢሕአዴግ በላሟ ልጅ ይመሰላል። ከጎኑ እንዳንቆምና ያለም ባንኮችን ሎቢ እንዳናደርግ የኢሕአዴግ ደጋፊ ልንመስል ነው። አይተን እንዳላየን እንዳንሆን ደግሞ ያገር ህልውና ጥያቄ አለበት። የቅርብ ዘመን ታሪካችንን እንኳን መለስ ብለን ብናይ ይህ ትውልድ ሁለት ተመሳሳይ ፈተናዎች ገጥመውት እንደነበር ማስታወስ እንችላለን። አንደኛው በ1969ኙ የሶማሌ ጦርነት ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በኤርትራው ጦርነት ጊዜ ነበር። ሕዝባችን ያደረገው ምርጫ ከመንግሥቶቹ ጋር የነበረውን ቅራኔ ለጊዜውውም ቢሆን ወደጎን አርጎ ባገር ጉዳይ ላይ ተረባረበ። የግቤን ጉዳይ በዚያ ትይዩ የማስቀምጥበት ምክንያት አለኝ። ይኸውም የታሪክ ጠባሳና መጥፎ “ፕሬሲደንስ” ፈጥረን እንዳናልፍ ከመስጋት ነው።
የምን ፕሪሲደንስ ነው ደሞ?
ኢትዮጵያ በአባይ ውሀ ሳትጠቀም ለዘመናት ኖራለች። በአንፃሩ ደግሞ የሱዳንና የግብጽ ሕልውና የተመሠረተው በዚህ ወንዝ ላይ ነው። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የረባ የባለቤትነት መብትና ያጠቃቀም ፕረሲደንስ አልመሠረተችምና በወንዙ ላይ ሁነኛ ፕሮጀክት እጀምራለሁ ብትል የሱዳንንና የግብጽን ስምምነት ማግኘት ያስፈልጋታል። ያለም ሕግ እነሱን ይደግፋልና። ህልውናቸውን ለማስጠበቅ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እስከማወጅ የሚያደርስ መብት ይኖራቸዋል። ሰዶ ማሳደድ ይሏችኋል ይሄ ነው።

አባይ ጥሩ አስተምሮናልና ግቤ ወንዝን ሰደን ማሳደድ አንችልም። ስለሆነም ያለንን የባለቤትነትና የመብት ጥያቄ በማያወላዳ ሁኔታ የማረጋገጡ ጉዳይ ወሳኝ ነው። ለኤንቫይሮንሜንታሊስቶችና ለአሳዳሪዎቻቸው ግፊት ከተፈታንና መብታችንን አሳልፈን ከሰጠን ሀገራችን ሁነኛ ልማት ማካሄድ የምትችልበትን የመጨረሻ ዕድል አባከነች ማለት ይሆናል። ከመጨረሻው የድህነት እርከን ፈቅ ለማለት እንኳ ላንችል ነው ማለት ነው። ዛሬም ጎጅ ፕረሲደንስ ላለመክፈት እንጠንቀቅ። የውጭ ባላንጣዎቻችን ማለፍ የማይችሉትን መሥመር ዛሬውኑ እናስምር።

ይህን ስናደርግ ዴሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን በሀገራችን ለማስፈን ከኢሕአዴግ ጋር የምናደርገውን ትግል እየቀጠልን መሆኑ አነጋጋሪ እንኳ አይደለም። በኔ ግምት ሁለቱ እንቅስቃሴዎች አይጻረሩም። እንዴትና በምን መልኩ የሚለውን ልንወያይበት እንችላለን። የቱን ያህል አስጨናቂ ቢመስልም በጉዳዩ ላይ ጨዋ ውይይት ማድረግን ልንሸሸው አንችልም።
ፀጋዬ ሙሉሸዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥሩ ጽፏልና አንብቡለት። http://www.ethiomedia.com/adroit/2431.html

kuchiye@gmail.com

No comments: