Wednesday, October 28, 2009


የ2010 ምርጫና ቻቻታው!

ከ2010 ምርጫ ጋር በተያያዘ ፊት-ለፊትና በሠያፍ የሚወረወሩት ትችቶች ብዛታቸውም ግለታቸውም እየጨመረ መሄዱ በመሀላችን የሰፈነውን የመረበሺና የጥርጣሬ ስሜት ያመለክታል። ስጋቱ ማንንም ከማን የለየ አይደለምና ትንሺ ልተችበት ፈለግሁ።

በኢሕአዴግ ልጀምር...
“ነገሮች በቁጥጥሬ ሥር ናቸው!” የሚል ገጽታ ማስተጋባት የሚፈልገው ኢሕአዴግ ውስጣዊ ጭንቀት እንዳለበት የፖለቲካን አቡጊዳን ለዘለቀ ሁሉ ስውር አይደለም። በ2005 ምርጫ ያደረሰው ጥፋት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማዳከም የሚያካሂደው ቅጥ ያጣ ዘመቻ፤ ሕዝብ የማስተባበር ችሎታ ያላቸውን መሪዎች ማሠሩና ማሳደዱ፤ ነጻውን ፕሬስ ማዳከሙ፤ ፍትሀዊ የምርጫ ሜዳ የለም ብለው ተቃዋሚዎች ባይካፈሉ የሚደርስበት ኪሣራ፤ ብቻውን ሮጦ አሸነፍኩ ቢል የውጭ መንግሥታት የገንዘብም የዲፕሎማሲም ድጋፍ ለመስጠት የመቆጠባቸው ጣጣ፤ የተዛባ ምርጫን ተከትሎ ሊመጣ የሚችል ቀውስ......እነዚህ ሁሉ ኢሕአዴግን ማስጨነቃቸው እርግጥ ነው።

የጠቀስኳቸው ዝርዝሮች በቂ አይደሉም የምትሉ ከሆነ ደግሞ ጥቂት ላክልበት እችላለሁ - በአሜሪካው ፀረ-ሺብር ዘመቻ ውስጥ ኢሕአዴግ የነበረው ተፈላጊነት መመንመኑ፤ ባፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ “ንብረትና ዕዳ” ሚዛን መዝገብ ላይ ኢሕአዴግ በዕዳው ዘርፍ መፈረጁ፤ ሀገሪቱን እያጥለቀለቀ ያለው የኤኮኖሚና የረሀብ ግሽበት፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዓለም መሪዎች መድረክ ላይ ቀዝቃዛ ትከሻ እያገኙ መሄዳቸው....እነዚህ ሁሉ ኢሕአዴግን እንቅልፍ መንሳታቸው ከቶውንም አያጠራጥር። ቁንጮ ላይ ያሉት ባለሥልጣኖች ደፍኖባቸው ቢሆን እንኳ አንዳንድ አስሊ ፖለቲከኞቻቸው ይህን አይስቱትም።

ወገኖቼ! ከላይ የተዘረዘሩት ጭንቀቶች ናቸው ኢሕአዴግን ከተቃዋሚዎች ጋር እንዲደራደር ያስገደዱት። ተቃዋሚዎችም ወደ ድርድሩ ያመሩት የመንግሥቱን አጣብቂኞች ከግምት አስገብተው፤ የፖለቲካ ኮንሴሺኖች እንደሚኖሩ አምነው፤ አጋጣሚው የነርሱን ራዕይ ልዑዋላዊነትና የኢሕአዴግን ፕሮግራም ክስረት ለማሳዬት ያመቻል ብለው ነው። በየትኛውም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሚዛን ላይ ብናስቀምጠው ተቃዋሚዎቹ ማለፊያ ስሌት አድርገዋል።

ስለ ስሌት ካነሳን ዘንድ የኢሕአዴግ አመራር ፍጹም ወጥ የሆነ አመለካከት አለው ብሎ መደምደም ስህተት እንደሆነ ሳላመላክት አላፍም። መንግሥት ከህዝብ ጋር እየተራራቀ መሄዱና ባጠቃላይ አገሪቱ ያለችበት አሳዛኝ ሁኔታ የሚያሳስባቸውና ለውጥ ማየት የሚሹ ግለሰቦች/ቡድኖች መኖራቸው ሊያከራክር አይገባም። ጥያቄው ቁጥራቸውና የኃይል ሚዛናቸው ተፈላጊውን ለውጥ ማምጣት ከሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል አልደረሰም ከሚለው ላይ ብቻ ነው። ኢሕአዴግ በጥቅል ሲታይ ጫካውን ከዛፉ ለይቶ ማየት የተሳነው፤ የፍልስፍና ችኮነትና የ “ስኬታማነት” እብሪት ጠላቶቹ የሆኑት መንግሥት ይመስለኛል። እነዚህ ሁለቱ ደግሞ የብዙ መንግሥታት መጥፊያ (ወተርሉ) ለመሆናቸው የኛም ያለም ታሪክም ይመሰክራሉና ኢሕአዴግን ከንቅልፉ የሚያነቃው “ደብል-ኤስፕሬሶ” ያስፈልገዋል እላለሁ።

ወደ ተቃዋሚው ልሸጋገር?
ተቃዋሚው ወገን በሁለት ጎራ ሊከፈል የሚችል ይመስለኛል። ጎራ-አንድ “ኢሕአዴግ ከመሣሪያ ትግል ውጭ አይሞከርም፤ የሠላማዊ ትግሉ ምዕራፍ አክትሟል፤ ገዥው መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሂዳል ማለት ዘበት ነው” የሚለው ነው። የሳይበር ደጋፊዎቹ ቻቻታ አስተማማኝ መለኪያ ይሆናል ብንል ይህ ጎራ “ሠላማዊ ትግል” ብሎ አገር ውስጥ ለሚንቀሳቀሰው ወገን ብዙም አድናቆት ያለው አይመስልም። በጎራ-አንድ ደግፊዎች እይታ ያገር ውስጦቹ ፓርቲዎች ወይ ባንዳዎች ናቸው ወይንም ደግሞ ባንዳ ለመሆን የተሰለፉ ናቸው። እንዴ! ይሄ ፍረጃ የሚባለው ነገር ጊዜው ያለፈበት ርካሺ የግራ ፖለቲካ ቅሪት መስሎኝ? ያሁኑን ዘመን ፖለቲካ እኮ በነጭና በጥቁር ብቻ ፈርጀው የሚያዩት አይደለም። “እኔ ልክ አንተ ስህተት” የሚባልበትም አይደለም። እመሀል ላይ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መስክ መፍጠር ነው አሸናፊ ፖለቲካ የሚባለው። ስለዚህ ተቃዋሚው ወገን ዓይን ላይን መተያየትን ሊለምድ ይገባል፤ ሊከባበር ያስፈልጋል፤ አንዱ የሌላውን ስብራት ለማገም በጎ ፍቃድ ማሳየት አለበት። እዚህ ላይ የመሪዎቹ ምሳሌ መሆን እስከታች የሚዘልቅ መልዕክት ያስተላልፋልና የመጀመሪያውን ርምጃ ሲወስዱ ማዬት እንፈልጋለን። “ሁሉም ዜሮ ዜሮ” ዓይነት ፖለቲካማ ይብቃን።

ጎራ-ሁለት ደግሞ “ሠላማዊ እንጅ ትጥቅ ትግል ለማካሄድ አመች አገራዊና ዓለም-አቀፋዊ ሁኔታ የለም” ባይ ነው። በተጨማሪም ኢሕአዴግን መግጠም በሠለጠነበትና በተካነበት የመሣሪያ ትግል ሳይሆን ፍጥጥ ብሎ የሚታየውን ደካማ ጎኑን ዕለት ተለት በማጋለጥ፤ ደንጊያ እንደምትሰብረዋ የዝናብ ጠብታ ያልታከተ የፖለቲካ ሥራ በመሥራት ነው ይላል። በሁለቱ ተቃራኒ አቋሞች ላይ ብዙ ስለተጻፈ በዝርዝር አላሰለቻችሁም። ስለ ግል አመለካከቴ “ሠላማዊ ወይስ ጥጥቅ - እንካስላንቲያዎቹ” በሚል ርዕስ የጻፍኩትን ማንበብ ትችላላችሁ።

የጎራ-ሁለት ደካማ ጎን አምስት ዓመት እንኳ ዕድሜ ያላስቆጠረ ብላቴና መሆኑ ነው። ስለሆነም የልምድ ማነስ ቢታይበት ልንበረግግ አይገባም። የዚህ ዓይነቱ ትግል አራማጆች ፈተና ብዙና ውስብስብ ነው። የሚመሩባቸውን ሰነዶች የማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ግልጽ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ደጋፊያቸው በሰቀቀን ኑሮ ውስጥ የሚገኝ ነውና ዛሬውኑ ውጤት ውለዱ ይላቸዋል። ሥራቸው ፊትለፊት ነውና ለነቀፋ፤ ለሴራና ለወከባ የተጋለጡ ናቸው። የሚጋፉት ካዝናውንም ወታደሩንም ሚዲያውንም ፍርድ ቤቱንም የግሉ ካደረገ መንግሥት ጋር ነው። በየድርጅቶቻቸው ውስጥ ሊመሠርቱ የሚሞክሩት የዴሞክራሲ ባሕል ለብዙዎች ባይተዋር ስለሆነ የግጭትና አንዳንዴም የመሰንጥቅ ጣጣ ያመጣባቸዋል። ከሥራው ጠባይ ጋር አብሮ የሚጓዝ መሰናክል ስለሆነ እንዴት እንደሚዘሉት ብቻ ነው ማሰብ የሚችሉት። ሊያስወግዱት ግን አይሆንላቸውም። እንዲህ ዓይነቱን የኃላፊነት ፈተና ለመቀበል የቆረጡ ወገኖቻችንን መደገፍ ባንችል እንዴት ልናከብራቸው እንቸገራለን?

የ “አንድነት” እና የ “መድረክ” ጉዳይስ?
“ቻተር” ይሉታል ፈረንጆቹ። የተሻለ ትርጉም የሚነግረኝ እስኪመጣ ድረስ “ቻቻታ” ብየዋለሁ። የሳይበሩ ሕብረተሰብ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚያደርገው ቻቻታ ከተጧጧፈ ያ ጉዳይ አሳስቦታል ማለት ነው። ያሳሳቢነቱ ደርጃ የሚለካው ደግሞ የተወሰኑ ቃላቶች ድግግሞሺ ሲበዛ ነው። የሀበሻውን ድረ-ገጽ ላንዳፍታ ብትቃኙት “አንድነት” “መድረክ” እና “ምርጫ” የሚሏቸው ቃላት ድግግሞሺ ጣራ ነክቷል። ለምን? ማለት ጥሩ ነው። እስቲ “ምርጫና አንድነትን” እንዲሁም “አንድነትና መድረክን” ላንዳፍታ እንመርምራቸው።

ምርጫና አንድነት። አንድነት ከመነሻው ሠላማዊ ትግል አካሂዳለሁ ብሎ ያወጀ ድርጅት ነውና ስለ2010 ምርጫ ቢያወራ፤ መግለጫ ቢሰጥ፤ ከመንግሥትና ከመንግሥታት ጋር ቢደራደር፤ ስትራቴጅያዊና ታክቲካዊ ጥቅም ባየበት ቦታ ከሌሎች ጋር ቢሻረክ ፍጹም መብቱ ነው። የሚጠበቅበትም ነው። ከነዚህ ተግባሮች ሊታቀብ የሚችለው ሥርዓትን በተከተለ መልክ በአባሎቹ በሚደረግ ውሳኔ ብቻ ነው። የሠለጠነው አገር አሠራርም የዴሞክራሲ ወግም ከዚህ የተለየ አይደለም። በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥና ዙሪያ የተሰባሰቡ ግለሰቦች በአንድነት የፖለቲካ ምርጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ተጽእኖ የማድረግ ሕጋዊም ሞራላዊም ሥልጣን እንደሌላቸው ቢረዱ ጥሩ ይመስለኛል። እነዚህ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው የራሳቸውን ቤት የማጠናከርና የማሳመር ብርቱ ኃላፊነት እያለባቸው ስለሌላው ቤት ለምን እንደሚጨነቁ ግራ የምጋባበት ጉዳይ ነው።

አንድነትና መድረክ። ተሳስቼ ከሆነ እታረማለሁ እንጅ በመድረክ መቋቋም ፀጉራቸውን ሲነጩ የማየው በሰላማዊው ትግል ዙሪያ ያሉ ፖለቲከኞች አይደሉም። “አንድነት ፓርቲ የብሔር ቅኝት ካላቸው ድርጅቶች ጋር ትብብር መፍጠሩ የስህተትም ስህተት ነው” እያሉ የሚደሰኩሩትም ከጥቂቶቹ በስተቀር የፓርቲው አባል ያልሆኑ፤ በደጋፊነት ደረጃ ተመዝግበው እንኳ የገንዘብም የሀሳብም አስተዋጽኦ የማያደርጉ ናቸው። ራስህን ዋቢ አደረግህ አትበሉኝ እንጅ በዚህ ርዕስ ላይም የጻፍኩትን http://kuchiye.blogspot.com/2009_07_01_archive.html ማየት ትችላላችሁ። ዘርዘር አድርጌ እንዳልተች በራሴ ላይ የጣልኩት የገጽ ገደብ ይዞኛልና በቅርቡ እመለስበታልሁ።

አንድ ነገር አስተውላችኋል? ልብ ብሎ ለተመለከታቸው ጥያቄዎች ብዙውን ጊዜ መልሳቸውንም አዝለው ነው የሚጓዙት። እስኪ በተረፉኝ መስመሮቼ ጥቂት ጥያቄዎች አንስቼ ልሰናበታችሁ።

1. በቅርብ ዘመን ታሪካችን ድርጅቶችና ፓርቲዎች ሕብረት፤ ጥምረት፤ መድረክ መፍጠራቸው ትዝ ይለናል። የውጤታማነታቸውን ነገር ለጊዜው ወደጎን ብንተወው በመተባበራቸው ምክንያት ደም ፈሶ አይታችኋል?
2. መተባበር ቀርቶ መነጋገርን አሻፈረን ያሉ ድርጅቶች ጦር በመማዘዛቸው ትውልድ እንዳለቀ ረስተነው ይሆን?
3. የመድረክ መቋቋም የተራራቁ አቋሞችን ለማቀራረብ፤ የጥርጣሬ ቀዳዳዎችን ለመዝጋት፤ የርስበርስ መተማመንን ለማዳበር ከመርዳት ሌላ ምን የሚያስከትለው ጠንቅ አለ?

Kuchiye@gmail.com.

1 comment:

Ashebir Neqatibeb said...

"kesatnu wuC maseb" malet demo mn malet new? If you cant write in amharic do it in English buddy!