Monday, April 20, 2009

"ከተለየኸን ደህና ሁን!"
ለጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ ሙት መሆኔን አገር ያውቃል። የርሱ ሙዚቃ ዳግም ላይሰማ ይታገዳል ያሉኝ ይመስል ከሰሞኑ መልሼ መልሼ የማዳምጠው ጥሌን ብቻ ነበር።

እንደኔ ሙዚቃን የሚያሻምድ ሰው ጥላሁን ለትውልዳችን የተሰጠ ልዩ በረከት፤ የዕምነታችንና የሁሉም ዓይነት ምኞታችን መገለጫ ነው ብሎ ከደመደመ ቆይቷል። አጋነንክ የሚል ከመጣም እስከመጨረሻው እሞግተዋለሁ እንጅ እንደ ሉሲና እንደ አክሱም ሀውልት ብሔራዊ ቅርሳችን ነው ባይ ነኝ። ለዚህ ይመስለኛል የጥላሁን ዜና-ዕረፍት እንደተሰማ ሚሊዮኖች በመብረቅ የተመታ ያህል ባሉበት የደረቁት፤ ያነቡትና የተከዙት።

የኔው ድንጋጤና ሀዘን ግን ወደ ፍስሐና ወደ መስጋና ሲለወጥ ፋታ አልፈጀበትም። ልማድ ሆኖብኝ ሲከፋኝና ፍቅር-ፍቅር ሲለኝ ኮምፒውተሬ ላይ ዘወትር በተጠንቀቅ የሚጠብቀውን የጥሌን ሙዚቃ ነው ጠቅ የማደርገው። ዛሬም ያንኑ አደረግሁና ወደ ትራክ ስድስት መራሁት። የሙዚቃው አጀማመር ገና ከመነሻው ምድርን ቃጤ የሚያደርግ ዓይነት ነው፤ በጣም የተሟሟቀ፤ የጥድፊያ ጥሪ ያለበትም የሚመስል…...ጥሌን የሚጣራ የሚመስል። ወዲያው ተቀላቀሉ ጥሌና ሙዚቃ…..ይለቀው ጀመራ በዚያ መረዋ ድምጹ!

“ያሳለፍነው ዘምን ደስታን ያየንበት…….ተመልሶ ቢገኝ አሁን ምን አለበት”
እ….ህህ! እህ..እህህ! አይይይይ!

ይሄን ሙዚቃ ስንቴ እንደሰማሁት የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው። ጥላሁን እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ኖታዎችን አዋህዶ የዘፈነበትና የድምጹ ቅላፄ ጐልቶ የወጣበት በዚህ ዘፈን ይመስለኛል። ቢሮዬ ወዲያው ተሟሟቀ። ለቀቅሁት እኔም እንዳቅሜ… አጀብኩት ጥሌን። ቢሮዬ ውስጥ ማን ለሲማኝ? ምድረ ፈረንጅ “ምን ተፈጠረ?” ብሎ ቢመጣም በቂ ምክንያት አለኝ አልኩ። የከበረና የተባረከ ህይወትን እየተሰናበትሁ ነው ካልኳችው እንደሚገባቸው አልተጠራጠርኩም። መቼም ፈረንጆች አይደሉም? ቀጠልን እኔና ጥሌ!.. “እ….ህህ! እህ..እህህ! አይይይይ!” አልን። ስንቱን ባነሆለለ ፈገግታው አየት ያደረገኝና “ቀጥል! ጥሩ ይዘሀል!” ያለኝ መሰለኝ ምን ገዶኝና ማንን ፈርቼ? ቀጠልኩ የጥሌን ትዝታና ውለታውን በልቤ እየመዘገብሁ።

ይሄ ነው እንጅ አልኩ! እንዲህ ነው እንጅ ጥሌን ማስታወስ። 55 ዓመት ሙሉ የምድረ ሀበሻን ቤት በደስታና በፈንጠዝያ የመላ፤ ያሳቀ፤ ያስደለቀ፤ መድረኮችን ያስጨነቀ፤ የወደደና ያዋደደ። ሺኝቱ በተለየ መሆን አለበት አልኩ። ልንሸነው የሚገባው በትዝታ ቅኝት፤ በባቲ ለዛ፤ ባንች-ሆየ ቃና፤ በ “ሠላመካ” ዝማሬ መሆን አለበት ብዬ ወሰንኩ። የ “አልቻልኩም”ን ጀግና፤ የ “ይህ ነው ፍላጎቴን” መሪ-ጌታ የምንሸኘው ከበሮው እየተደለቀ፤ ሳክሱ እየሳቀ፤ ትራንፔቱ እያማለለ ሊሆን ይገባል አልኩ።

ጥላሁን ዝንተ ዓለም አይረሳም። መሰል-የለሺ እንጉርጉሮዎቹን፤ ግርማ ሞገሱንና የርሱ ብቻ የሆነ ለዛውን በውስጠኛው የምናባችን ክፍል አትሞብናልና። የዘመናችንን የኪነት የበህር ልጅ እንዴትስ ልንረሳው ይቻለናል?

በል ደህና ሁን ጥሌ! ከተለየኸን… ደህና ሁን!
Kuchiye@gmail.com

http://www.voanews.com/horn/amharic_audio.cfm