Friday, April 16, 2010

"ዱድ! ብሩን አሳዬኝ!" Dude, Show Me the Money!


በውጭ የሚኖረው ወጣት ባገሩ ፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ አለመሆኑ ያሳዝነኛል። አንዳንዴማ ከዚያም ያለፈ ነው የሚያደርገኝ። ሰሞኑን ታዲያ ጃዋር ሲራጅ መሀመድ የተባለ ኦሮሞ ወገኔ ተስፋ ዘራብኝ።

ዲሲ በተካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ ነው የ24 ዓመቱ ጃዋር “ዱድ” ሥራውን ሲያቀርብ ያዳመጥሁት። የነጠሩ ሊቆች የሚወጡበት የስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ ነውና የዋዛ 24 ዓመት እንዳይመስላችሁ። ባንፃሩ ደግሞ ከጃዋር ጋር መድረክ የተጋሩት ምሁራን ባገራችን ፓለቲካ ውስጥ ቆይታ ያደረጉ፤ የቤታችንን ግድግዳ ጌጦች ያህል የምናውቃቸው ባለውለታዎቻችን ነበሩ። እዚህ ላይ በጃዋርና በሌሎቹ መሀከል የነበረው የዕድሜ ልዩነት ከልክ በላይ እንዳስደመመኝና ጥያቄዎች እንደጫረብኝ ልደብቃችሁ አልችልም። ያነሳቸው ነጥቦች ጆሮዬ ላይ ሲዘምሩብኝ ነው የከረሙትና ላከፍላችሁ ብዕሬን አነሳሁ።

ሦስት ቀን ስለፈጀው ዓውደ ጥናት ባንዲት አንቀጽ ውስጥ ጥቂት ልበልና ጃዋር በምሳሌነት እንዲያገለግለኝ ወደመረጥሁት ወደ ወጣቱ ጉዳይ እመለሳለሁ። ያለጥርጥር እጅግ የተሳካ ስብሰባ ነበር። አዘጋጆቹ ብዙ ጉልበት እንዳፈሰሱበት የሚመሰክሩ አሻራዎች ስላየሁ አብዝቼ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። አቅራቢዎቹም፤ ታዳሚውም ሀላፊነታቸውን ሲወጡ ያየሁት ፍጹም በሰከነ ቋንቋና በደርባባ ባህርይ ስለነበር ስልጡን ፖለቲካ ተገቢ ቦታውን እያገኘ ነው አልሁ። ታዲያ በባህላችን “ግን” ካልተጨመረበት ምስጋና ምስጋና አይሆንምና ለወደፊቱ ይታሰብበት ዘንድ ላዘጋጆቹ ትንሺ ቅር ያለኝን ነገር ላካፍላቸው እወዳለሁ። የኢትዮጵያ ችግር በርካታ ሆኖባችሁ ይመስለኛል ሁሉን ርዕስ ለመሸፈን ባደረጋችሁት ሙከራ ዓቢይ ጉዳዮች ላይ ሊያወያዩን የመጡ ምሁራን ሰዓት እያነሳቸው ነገራቸውን እንዲቆራርጡ መገደዳቸው አሳቆኛል። ያቅራቢዎቹን ቁጥር ሰብሰብ ማድረግ ቅያሜ የሚያስከትል ሆኖባችሁ ይሆን?

የጃዋር አቀራረብ የወጣት ለዛና የወጣት ነፃ አስተሳሰብ የተንጸባረቀበት ነበር። በዝግጅት ደረጃም የተሻለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ - ፓወር-ፖይንት ተክኖሎጅን ተጠቅሟል፤ የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ምን ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለ ለማስረዳት በቃላት ጋጋታና በ “እጠቅሳልሁ” “አልጠቅስም” አባዜ አልታሰረም። በአዕምሮ ውስጥ ታትሞ በሚቀር ቪዡዋል ቻርት አማካይነት በሁለት የፖለቲካ ጠርዞች ላይ የሚገኙትን አስተሳሰቦች ደህና አድርጎ ተንትኖ መፍትሔው መሀል ላይ መገናኘት ብቻ መሆኑን በሚገባ አስረድቷል።

በርሱ ስሌት በ “ብሔርተኛውም” ሆነ “ኢትዮጵያዊነት” በሚለው ካምፕ ውስጥ አክራሪ ዓይነት አቋም ያላቸው ከ 20% አይበልጡም። ቀሪው 80% ፍጹም ሠላማዊ ኑሮ ፈላጊና የብሔር ቅርሱን ለማዳበር የሚያስችል ሥርዓት እስካገኘ ድረስ በኢትዮጵያዊነት መለያው የሚኮራ ነው። “ሆኖም ግን በየመድረኩና በየቤቱ ከሚመነዘሩት የመልካም ምኞት መግለጫዎች ባሻገር ተጨባጭ ሥራ መሠራት አለበት” አለ።

“ፈተናው እዚህ ላይ ነው ወገኖቼ! አዲሱ ትውልድ ለዙሪያ ጥምጥም ፍልስፍና፤ ለዲስኩርና ለቃላት ማንጠር ትዕግሥትም አንጀትም የለውም” ሲል አስጠነቀቀ ጃዋር ድምጹን ከረር አድርጎ። አውራ ጣቱንና የታጠፈች ሌባ ጣቱን ሕዝቡ እንዲያይለት ከፍ አድርጎ ደጋገሞ እያፋተገ “ይህ ትውልድ የ ሾው-ሚ-ዘ መኒ! ትውልድ መሆኑን መቀበል አለብን!” አለ። ጭብጨባውና ቻቻታው መለኪያ ከሆነ በዚያች ወቅት የታዳሚውን ቀልብ ሙልጭ አድርጎ ኪሱ እንዳስገባ አልጠራጠርኩም። ለዚህም ነው “ዱድ! ብሩን አሳዬኝ!” የምትለዋን የጽሑፌ ርዕስ ያደረግኋት።

ጃዋር “ሾው-ሚ-ዘ መኒ!” ሲል ወጣቱ ትውልድ እንደሸቀጥ በገንዘብ የሚገዛ ነው ለማለት አልነበረም። “ባዶ ቃላት አትመግበኝ! ከዚህ የጥርጣሬ ዘመን ወደመተማመን ዘመን እንዴት እንደምንሸጋገር ያለህን ተጨባጭ የመፍትሄ ሀሳብ እፊቴ ቁጭ አድርግልኝ” ማለቱ ነበር። የጃዋር ትውልድ ባጠቃላይ፤ የአማራ/ትግሬ ዝርያ የሌለው ክፍል ደግሞ በተለይ፤ አዲሱ የኢትዮጵያዊነት ገጽታ በማያሻማና ቅሬታን በሚያጠፋ መልኩ ተነድፎ ሲተገበር መሳተፍ እንደሚፈልግ ጃዋር አሳውቋል። ይህን ዕውን ለማደረግ የሚወሰዱ ርምጃዎችም በዕለት-ተለት ግንኙነቶቻችን ሳይቀር የሚንጸባረቁ መሆን እንደሚገባቸው በአጽንኦት ነበር ያስረዳው። ነጥቡን ለማስረገጥ መሰለኝ፤ መድረኩ ላይ ከርሱ ጋር የተሰየሙትንና ዞር ብሎም ታዳሚውን ሕዝብ በዓይኑ ቃኘት አድርጎ “ይህ ፎቶግራፍ ኢትዮጵያዊነትን በቅጡ ስለማንጸባረቁ እርግጠኛ አይደለሁም” አለ።

በዚህ ጊዜ ነበር የጉባዔው አዘጋጆች ወደ መድረኩ ብቅ ብለው በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያገባቸውን ሁሉ መጋበዛቸውን የገለጹት። በድረ ገፆች አማካይነት ከተደረገው ግልጽ ግብዣ በተጨማሪ ካንዳንዶቹ ጋር ቀጥታ ግንኙነቶች ተደርጎ አመርቂ ምላሺ እንዳልተገኘ አስረዱ።

እዚህም ላይ “ሕምምም!” ያሰኘ ቅጽበት ተፈጥሮ ነበር። ጃዋር ያዘጋጆቹን ጥረት አድንቆ እርሱ ራሱ ጉባኤው ላይ ቢገኝ ምን ዓይነት ምቾት እንደሚሰማው ጥርጣሬ አድሮበት እንደነበረ ተናዘዘ። ሆኖም ግን ላቀረባቸው ነጥቦች ሕዝቡ ይሰጠው የነበረውን ከበሬታ ካዬ በኋላ በውሳኔው እንደኮራ አልሸሸገም። በመቀጠልም “የቀሩት ወገኖቻችን ካልመጡ ከመንገዳችን ወጥተን የምናደርገው የማግባባትና የማረጋጋት ሥራ በቂ አልነበረም ማለት ነው” ብሎ በዚህ ረገድ ብዙ እንደሚቀረን አስተማረ። ይህ ሰው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገና ብዙ ሚና እንደሚኖረው፤ በዕድሜም በብሔሩም በዕምነቱም እርሱን መሰል ዜጎችን በመሳብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጻኦ እንደሚያደርግ ፍንትው ብሎ ነው የታየኝ።

በዚህ ስብሰባ ላይ ወጣቱን ትውልድ ወደፊት የማምጣቱ አስፈላጊነት አንገብጋቢ እንደሆነ በብዛት ተወስቷል። የ 24 ዓመቱ ወጣት 55+ ሶች ጋር መቅረቡ ነው ጥያቄውን ከምኔውም በበለጠ ትርጉም የሰጠው። አንዳንዶቹ አቅራቢዎች ይህን ጉዳይ ሲያወሱ ጥፋት እንዳጠፋ ሰው መሸማቀቅ አይቸባቸዋለሁ። በዚህ ፈጽሞ አልስማማም። የቀድሞዎቹ ብዙ መሥዋዕትነት ለመክፈላቸውና ብዙ ለማስተማራቸው አጠያያቂ አይደለም። በወቅቱ ተረካቢ አለማፍራታቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ወንበር የሙጥኝ ማለታቸው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወጣቱን የሚስብ ራዕይና የሚጥመው አሠራር አለመንደፋቸው ጥፋት ነው። አባጣ ጎባጣ ያልበዛበት የትውልድ ሺግግር ሳያደርጉ በየጓዳቸው ቢከተቱ ግን የጥፋትም ጥፋት ይሆንባቸዋል። ስለዚህ እስቲ ፈረንጆቹ “ሜንተርሺፕ” የሚሉትን ነገር ይሞክሩት። ያንዳንድ ወጣት እጅ ይያዙ።

ወደ ጃዋር ልመለስና። በቃላቶቹም ቃላቶቹን ባጀቡት ስሜቶችም አዲስ የኢትዮጵያዊነት ራዕይ መቀረጽ እንዳለበት ነው አበክሮ ያስተማረው። ለምን በሉ? እንደርሱ ባሉ ወገኖቻችን መንደር እስከዛሬ የምናውቀው “ኢትዮጵያዊነት” በሰሜኑና በደገኛው ባህል እንዲሁም በዚያ ሕዝብ ሳይኪ ዙሪያ የተገነባ ነውና ሌላውን ጮቤ ሊያስረግጠው መጠበቅ የለበትም። ባመዛኙ እንዲያገለግልም እንዲያኮራም የተደረገው የዚያኑ የሰሜን ደገኛ ሰው ስለሚመስል አንዳንዴ ቁጣ ቢያስነሳም መገርም እንደሌለብን ቃላት ሳይልቆጥብ ተናገረ። ከቶውንም “ና በድሮው ኢትዮጵያዊነት ዙሪያ እንሰባሰብ ብትለኝ አይመቸኝምና አቤት ለማለት አልጣደፍም” ነበር ያለው። እንዴ ካልተመቸው ምን ይበል?

እንግዲህ ያልሆነ ትርጉም ለመስጠትና አጉል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አትጣደፉ! ጃዋር በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን፤ የነገው እንጅ ያለፈው ብዙም ፋይዳ እንደሌለው የተረዳ፤ ነገር ግን አዲሱ የኢትዮጵያዊነት ራዕይ አንዱን እላይ ሌላውን እታች በማያደርግ መልኩ በድፍረትና በስልት መቀረጽ እንዳለበት ነው ያሳወቀው። ዜጎችንና ብሔረሰቦችን የሚያቀራርብ፤ መተማመንን የሚያሰርጽ ድልድይ በያቅጣጫው ተዘርግቶ ባዲስ ጥርጊያ መንገድ ጉዟችንን እንድንጀምር ነው የሚመኘው። ችግራችንን በሠላማዊ ትግልና ተጨባጭ ርምጃዎች በመውሰድ እናስወግድ ነው የሚለው። ለኔም ለናንተም ጆሮ ከዚህ የተሻለ ጥዑም ሙዚቃ አለ?

ጃዋር የመጀመሪያውን ርምጃ ወስዷል፤ እኛስ ጎረቤታችንና ሥራ ቦታ ከምናገኘው ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ ወላይታ፤ ሀረሬ አማራ..ወዘተ ጋር ለመቀላቀልና ለመወዳጀት ከመንገዳችን ወጥተን ሙከራ እያደረግን ነው? (አዎንና! ከመንገዳችን ወጥተን!) እውነተኛ ፍቅር የተመላበት ፈገግታ እየሰጠናቸው ነው? እንድንመቻቸው እያደረግን ነው? ጃዋር አዘጋጆቹን ያሳሰበውን አትዘንጉ። “እኛ ግብዣ አስተላልፈንላቸዋል መምጣት የነርሱ ፋንታ ነው ብላችሁ መቀመጥ የለባችሁም” ነበር ያላቸው። ካስፈለገ እጃቸውን ጎትታችሁም እንደማለት ጭምር መሰለኝ። ዕውነት አለው ወዳጄ!

የጃዋርን ዋና ቁምነገር አትርሱ። ወደድንም ጠላንም አዲሱ ትውልድ መድረክ ላይ ብቅ እያለ ነው። የተፈጥሮ ግዴታ ጭምር ነውና። አዲሱ ትውልድ ደግሞ የ “ሾው-ሚ-ዘ መኒ!” ትውልድ ነው። ከተስፋ ይልቅ ተጨባጭ ርምጃ፤ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፤ ከቃላት ጋጋት ይልቅ ቅልጥፍ ባለ ቋንቋ እንድናወጋው ነው የሚፈልገው። ለሚንዛዛና ለቃላት አንጥረኛ ጊዜ የለውም። ለርሱ ጊዜ ወርቁ ነው።

የምወዳቸውና የምኮራባቸው የራሴ ልጆችም የጃዋርን መሥመር በጣሙን እንደሚጋሩ ገልጸውልኛልና ነገሩ ዕውነት ሳይኖረው አይቀርም ወዳጆቼ!

kuchiye@gmail.com

1 comment:

Dr. Tsehaye Zemenfes said...

Hello Kuchiye,
Thank you for the great analysis about the talented brother. I have actually met him at the meeting in DC and he is quite fascinating. I myself, of his generation, very much been interested in the politics of the motherland.

I have always argued that we are the generation that can take Ethiopia in a different route but most of us have been shun out by the old generation, who are still on their operation of revenge by creating havoc. I hope in the near future young people like myself will reach out to the different young Ethiopians and get them to be interested in the politics of Ethiopia in a very meaningful and creative way. We have to be able to cultivate talented people to assume leadership in the near future.

Myliham