Thursday, April 01, 2010

ተቃዋሚው ብቃት አለው? - “Is the Ethiopian Opposition Viable?”


በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ ጥርጣሬ የመፍጠርን ያህል የፕሮፓጋንዳ ድል የለም። ለዚህ ማስረጃ ከፈለጋችሁ የሂትለር ቀኝ-እጅና የፕሮፓጋንዳ ጠበብት የነበረውን ጎብልስን ጠይቁት። ዓለም ሲፈጠር የት ነበርክ ትሉኛላችሁ እንጅ ከያን ጊዜ ጀምሮ ይመስለኛል ጥርጣሬ መፍጠር የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ የሆነው።

ቀልጠፍ ብዬ ወደተነሳሁበት ርዕስ ልመለስና “በርግጥ ተቃዋሚው አገር የመምራት ብቃት አለው?” የሚል ጥያቄ መናፈስ የጀመረው በ‘97 ምርጫ ማግስት እንደነበር ትዝ ይለኛል። ቅንጅት ውስጥ በተፈጠረው ውዝግብ ቆሺታቸው ያረረ ደጋፊዎች ሳይቀሩ ነው አባባሉን የብስጭታቸው መወጫ ያደረጉት - ትልቅ ስህተት! በጣም ትልቅ ስህተት! ኢሕአዴግ ደግሞ እንኳንስ ይችን ያህል ቀዳዳ አግኝቶ እንዲያውም እንዲያው ነው በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን የጥርጣሬና የብሺቀት መንፈስ ደህና አድርጎ አራገበው።

እዚህ ላይ ባንድ ነገር እንስማማ። የሰው ልጅ በፍጥረቱ ተጠራጣሪና የ7 ቀን 24 ሠዓት ኑሮው በስጋት የታጠረ መሆኑን አትክዱኝም። ለዚህ አይደል እንዴ ኢንሹራንስ የሚገዛው? አጥር የሚያጥረው? ብቻውን የሚያወራውና የሚቃዠው? ልብ ብላችሁ ከሆነ ፖለቲከኞች ይህን ሰብዓዊ ደካማ ጎን ደህና አድርገው ነው የሚበዘብዙት....

“ነውጠኞች የቀድሞውን ሥርዓት ሊያመጡብህ ነው! እኛ ከሌለን አገር ትበተናለች! ሠላማዊ ኑሮህ ይናጋል! የብሔረሰቦች ነጻነት ይገፈፋል! የርስ በርስ ጦርነት ይነሳል! የስልምና አክራሪዎች አገርህን ይወሩታል! ተቃዋሚው አገር የማስተዳደር አቅም የለውም!”


የኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ መዘውር ከላይ ለአብነት የጠቀስኋቸውን የስጋት መርዕዶች በመደጋገም እንደሚጠቀምባቸው እናውቃለን። “በመደጋገም” የምትለዋን ቃል እንደዋዛ አትዩብኝ። በፕሮፓጋንዳ ሳይንስ “ስጋት” ታላቅ ወንድም ቢሆን “ድግግሞሺ” ደግሞ ታናሹ ነው። እዚህ ላይ የኢሕአዴግ ዘመቻ በኢትዮጵያ ውስጥ የስጋት ድባብ አልፈጠረም የሚለኝ ቢመጣ “አንተ የሰጎኗ ወንድም ነህ!” ከማለት አላስተርፈውም። ዕለት ተለት በስጋት አየር ውስጥ የሚኖሩት ወገኖቻችን ቀርተው ያሜሪካና ያውሮፓ መንግሥታትም የዚህ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጭዳ ሆነዋል። “ህምምም!” በሚያሰኝ ጥርጣሬ ውስጥ ለመውደቃቸው አንድና ሁለት የለውም። ራሳቸው ሳይደብቁ ይነግሩን የለም እንዴ?

ታዲያ ሁለት ዓቢይ ችግሮች ይታዩኛል። አንደኛው ችግር ተቃዋሚው ወገን የዚህን ፕሮፓጋንዳ አደገኛነት ተገንዝቦ ቀጣይነት ያለው አምካኝ ፕሮፓጋንዳ በፈረንጁ ሰፈር ጭምር አለማካሄዱ ሲሆን ሁለተኛው ችግር ደግሞ የተቃዋሚው የፖለቲካ ገጽታ በመንግሥት እንዲነደፍ መፈቀዱ ነው። በሁለቱም ላይ ያለኝን የተሙን ሀሳብ አካፍላችኋለሁ።

በደፋር አስተያየት ልጀምርና ይህ ዘመን ኢትዮጵያን ወደከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር ከምን ጊዜም የበለጠ ተነሳሺነት የገነነበት፤ የሰለጠነ የሰውና የማቴሪያል ኃይል የተከማቸበት ነው እላለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚው ክፍል፤ በተለይም “መድረክ” ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ያለው ብቃት ከየትኛውም ፓርቲና ስብስብ የላቀ ነው እላለሁ። እንዳላሰለቻችሁ በሦስት ዋቢዎች ብቻ ልወሰን።

የፖለቲካ ፕላትፎርም። የአንድነት/መድረክ ፖለቲካ ፕሮግራም የዜጎችን ችግር አበጥሮ የተረዳ ብቻ ሳይሆን ያጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎቻቸውንም የሚዘረዝር ነው። ያልተገደበ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንደሚኖር፤ የግል መሬትና ንብረት የሕገ መንግሥት ጽኑ ድጋፍ አግኝተው የኤኮኖሚና የማሕበራዊ እድገት አንቀሳቃሺ ሞተር እንደሚሆኑ፤ የኢትዮጵያ አንድነትና ልኡዋላዊነት ለድርድር የሚቀርብ እንደማይሆን፤ ብሔረሰቦችን የሚከፋፈል ፖሊሲ ተወግዶ ያንድ አገርና ያንድ ታላቅ ራዕይ ልጆች በሚያደርግ ፖሊሲ እንደሚተካ፤ 85ሚሊዮን ሕዝብ ህልውናውንና ስትራቴጅያዊ ጥቅሙን አደጋ ላይ በማይጥል መልክ ወደ ባሕር የመውጣት መብቱ እንደሚከበር፤.. ወዘተ ያስቀምጣል። ትናንት የቅንጅት ዛሬ ደግሞ ያንድነት የሆነው ራዕይ ገዥው ፓርቲ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ከሚለው ራዕይ በዓይነትም በጥራትም የተሻለ፤ እጅግ በጣም የተሻለ ለመሆኑ ሕዝብ በቅጡ ያውቃል። ለዚህ ነበር በ ‘97ቱ ምርጫ ቅንጅትን የሾመው። ለዚህም ነው ዛሬ በአንድነትና በመድረክ ዙሪያ በሚያስደንቅ ቁርጠኝነት እየተሰባስበ ያለው። ሌላውን ለጊዜው እንተወውና በትግራይ ክልል እየተገለጸ ያለው የፓራዳይም ለውጥ አላስደነቃችሁም? ጥልቅና የምሥራች ትርጉም እንዳለው አልተረዳችሁም?

በቢሮክራሲ ልቀጥል። ማንኛውም ለሥልጣን የሚበቃ መንግሥት ሀገሪቱ አዳብራ ባቆየችው ያስተዳደር መዋቅር (ቢሮክራሲ) መገልገሉ ሀቅ ነው። ይህ የጦር ሠራዊቱን ይጨምራል። ምኒልክ ከዮሐንስ፤ ኃይለ ሥላሴ ከምኒልክ፤ ደርግ ከኃይለ ሥላሴ፤ ኢሕአዴግ ከደርግ በተረከቡት ቢሮክራሲ ነው አገር የመሩት። ሌላው ሀቅ ደግሞ እያንዳንዱ መንግሥት የተረከበውን ቢሮክራሲ አሻሽሎና አዳብሮ ለሚቀጥለው መንግሥት የማስረከቡ ዕውነታ ነው። በዚህ ስሌት እንደ ኢሕአዴግ ጠንካራ መሠረት ያለው፤ በተማረ የሰው ኃይልና በዘመናዊ የማኔጅመንት ዘይቤዎች የዳበረ ቢሮክራሲ የወረሰ መንግሥት አልነበረም። ኢሕአዴግ ራሱ ምን ዓይነት የመንግሥት-አስተዳደርና የማኔጅመንት ልምድ ይዞ በ1991 አዲስ አበባ እንደደረሰ የያኔ ሬዙሜውን ማዬት ይበቃል። በራሴ ላይ የጣልኩት የገጽ ማዕቀብ ከለከለኝ እንጅ ከአፄ ዮሐንስ እስከ ኢሕአዴግ ያሉት መንግሥታት ሥልጣን ሲይዙ የነበረባቸውን ፈተና አነጻጽርላችሁ ነበር። ላለፉት መንግሥታት ከልብ ታዝኑላቸዋላችሁ።

እዚህ ላይ ያች ልማዴ እንዳትቀር አንዳፍታ ከመሥመር ወጣ ልል ነው። ስለ ቢሮክራሲ ካወጋን ዘንድ “ቢሮክራሲ” ከፍተኛ የሥም ማጥፋት ዘመቻ የተካሄደበት ያገር ኃብት ነውና ይህን የተዛባ አመለካከት ማቃናት አለብን እላለሁ። ካጭር ትርጉሙ ብንነሳ “ቢሮክራሲ” ያንድ ትልቅና ውስብስብ መዋቅር አስተዳደራዊ አቅም ነው። በሹመት እየመጡ አናት ላይ ጉብ ከሚሉት አላፊዎች በስተቀር ሌላው ሕዝበ-ሠራዊት በሙያ ሚዛን እየተለካ እንደሚቀጠርበት ግዙፍ አገራዊ ፋብሪካ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። መንግሥት ቢለወጥ፤ ሹም ከርቸሌ ቢወርድ፤ ጎርፍ ቢያጥለቀልቅ፤ ቢሮክራሲ ከቦታው ንቅንቅ አይልም። እንደ ዝቋላ ተራራና እንደ አዋሺ ወንዝ ካስቀመጡት ቦታ የሚገኝ ውሉን የማይስት ያገር ኃብት ነው ማለት ነው። ቢሮክራሲን ያልሆነ ጥላሸት የቀባው ባላባቱን፤ ከበርቴውን፤ ካፒታሊስቱንና ኢምፔሪያሊስቱን የሕዝብ ጠላት በማድረግ አንጀቱ ያልራሰለት የኮሚኒስት ሥርዓት ነበር። እንዲያው በሞቴ ኮሚኒስቶች የሚሉትን ከቁብ የሚጥፍ ሰው ተርፎ ይሆን?

በፓራዳይም ለውጥ ላጠቃል። ሦስተኛው ቁምነገር ደግሞ ለመድረክ መፈጠር ምክንያት የሆነ የፖለቲካ ክስተት መኖሩ ነው። የብሔር ፖለቲካ ከመሣሪያነት አልፎ ማቴሪያላዊም ሆነ ማህበራዊ ጠቀሜታ እንደማያስገኝለት ሕዝቡ መረዳት ከጀመረ ሰንበት ብሏል። መቼም ፖለቲከኞች ብልጥ አይደሉም? - የፓራዳይም ለውጥ ሕዝብ ውስጥ ሥር መስደዱን ከማረጋገጣቸው በፊት የአቋምና ያሰላለፍ ለውጥ አያደርጉም። ለዚህ ነው እንገነጠላለን ከሚሉት ጀምሮ ለዘብተኛ እስከሚባሉት ድረስ በብሔር ፖለቲካ ላይ ያላቸውን አቋም ሲከልሱ እያየን ያለነው። ዓለም ወደ አንድ ትንሺ መንደርነት እየተለወጠች በምትገኝበት በ 21ኛው ክፍለ ዘመን የብሔር ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎች ከሌላ ፕላኔት እንደመጡ ፍጡሮች ይቆጠራሉና መለወጣቸው እሰዬ የሚያሰኝ ነው። የብሔር ፓለቲካ ያራምዱ የነበሩ ፓርቲዎች በመድረክ ውስጥ መሰባሰባቸው፤ በብሔር ፖለቲካ ዓለም ውስጥ ስማቸው የተጠራ እንደነ ስዬ አብርሃ፤ ነጋሶ ጊዳዳ፤ ገብሩ አሥራት፤ አረጋሺ አዳነና ቡልቻ ደመቅሳን የመሳሰሉ በመድረክ ውስጥ መሰባሰባቸው አንዳንዶች ሊያምኑ ከሚፈልጉት በላይ ጥልቅ መልዕክት ያዘለ ነው። ባጋጣሚና በድንገት የተከሰተ ፓራዳይም ሳይሆን ከ 45 ዓመት ተመክሮ የተወለደ ነው።

እዚህ ላይ “ተቃዋሚው ኢትዮጵያን ለመምራት ብቃት አለው?” ከሚል ጥያቄ ጋር ምን አገናኘው ብትሉ አልፈረድባችሁም። አያችሁ! ኢሕአዴግ ባለሙያና ደጋፊ የሚጨልፈው የብሔር ፖለቲካን በውድም በግድም ከሚያራምዱ ቁጥራቸው እየቀነሰና ወርዳቸው እየጠበበ ከሚገኝ የህብረተሰብ ኩሬዎች ነው። ባንጻሩ ደግሞ መድረክ ደጋፊና ባለሙያ የሚቀዳው እጅግ ሰፊ ከሆነ የህብረተሰብ ሃይቅ ነው። ለዚህ ነው ተቃዋሚው ክፍል፤ በተለይም “መድረክ” ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ያለው ብቃት ከየትኛውም ፓርቲና ስብስብ የላቀ ነው ያልኩት - እመነሻዬ ላይ። የለየልኝ ቅን-አሳቢ መሆኔን ደጋግሜ ተናዝዣለሁና ቀሪዎቹ በብሔር ፖለቲካ ጠርዝ ላይ የሚገኙ ያገሬ ልጆች ከፊታቸው የተጋረደውን መጋረጃ እየቀደዱ አንድነትን፤ ኢትዮጵያዊነትንና ትልቅነትን እንዲያቅፉ እመኛለሁ።

ወዳጆቼ! ይችን ጽሁፍ ካነበባችሁ በኋላ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ በብስጭትም ሆነ በተንኮል ተነሳስታችሁ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ችሎታ ላይ የጥርጣሬ አሉባልታ ብታናፍሱ ባደባባይ እሞግታችኋለሁ። ሲናፈስም ዝም ብላችሁ ካያችሁ ለእሰጥ-አገባ ተዘጋጁ። የምሬን ነው!

No comments: